የቢሮ የኃላፊ መልዕክት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ

የማእከላዊ ኢትዮጰጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ነሀሴ 13/2015 ሲመሰረት የተሰጠው ዋና ተልዕኮ ጥራት ያለውና ውጤታማ የግል ኢንቨስትመንት በተለይም አምራች ኢንዱስትሪ በክልላችን እንዲስፋፋ በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው፡፡
ይህን ለማሳካት የሴክተሩን ተልዕኮ ሊወጣ የሚችል ተቋም በመገንባት፣ የክልሉን እምቅ አቅም እንዲጠና በማድረግ፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የክልሉ ፀጋ የሚለማበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ፣ ያለንን እውቀት፣ ክህሎትና፣ ቴክኖሎጂ በአግባቡ በመጠቀም ክልሉን በፍጥነት በማልማት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሃብ የማድረግ ህልም እውን ማድረግ ነው፡፡ በክልላችን ኢንቨስት አድርጋችሁ እራሳችሁንም ህዝቡንም መጥቀም የምትፈልጉ ኢንቨስተሮች ወደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንድትመጡ እንጋብዛለን፡፡
ክልሉ ከፍተኛ ወጣትና አምራች የሰው ሀይል ያለበት፣ ተባባሪ እና የመልማት ፍላጎት ያለው አመራርና ህዝብ ያለበት፣ ለአገር ውስጥም ለውጭም ዋና ዋና ገበያዎች ቅርበት ያለው፣ ለግብዓትነት የሚያስፈልጉ የግብርና ምርቶች በስፋት የሚገኝበት፣ መሬት በአነስተኛ ኪራይ ለረጅም አመት መከራየት የሚቻልበት፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ያለበት፣ ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሰጥበት ለኢንቨስትመንት የሚመች ክልል ነው፡፡ በክልሉ የተሰማሩ የአገር ውስጥ እና የውጭ ኢንቨስተሮች በአብዛኛው ስኬታማ የሆኑበትና ብዙዎቹም የማስፋፊያ ስራ እየሰሩ የሚገኙበት፣ በአነስተኛ የማምረቻ ወጪ ብዙ ማምረት የሚቻልበት ክልል ነው፡፡ በአጠቃላይ ክልላችን እንደ ስሙ ማእከላዊ አስተሳሰብ እና ሚዛናዊ እይታ ያለው፣ ታታሪ እና ኢንተርፕሪነር ህዝብ፣ በተለይ የሰለጠነ አምራች ወጣት በብዛት ያለበት ክልል ነው፡፡
ስለዚህ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኬሚካል፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎች፣ በመድሀኒትና የህክምና መገልገያዎች፣ በቱሪዝምና አገልግሎት የኢንቨስትመንት፣ በአይሲቲ፣ እና በሌሎችም ዘርፎች መሰማራት ለምትፈልጉ በራችን ክፍት ነው፡፡ መልእክታችንን ስላያችሁ እናማሰግናለን!
ዶ/ር አባስ መሐመድ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ















