የኢንደስትሪው ዘርፍ ለማስፋፋት በቂ መሬት መዘጋጀቱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር አባስ መሃመድ ገለፁ። ቢሮው ከዞንና ከልዩ ወረዳ ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት በማምረት አቅም ልኬት፣ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በዘርፍ ማህበራትና ምክር ቤት አደረጃጀት ዙሪያ በወልቂጤ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተጠናቀቀ። የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንት እና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አባስ መሃመድ እንዳሉት የኢንደስትሪውን ዘርፍ ለማስፋፋትና ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም ለማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በእውቀት መምራት ያስፈልጋል። በመሆኑም ቢሮው የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች በኢንዱስትሪ ጠቀሜታ፣ በአካባቢ ብክለት መከላከልና በሌሎች ዘርፎች ላይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው ዘርፉን ለማነቃቃት እንደሚያግዝ ገልጸዋል። መንግስት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከጀመረ ወዲህ በሃገር አቀፍ ብሎም በክልል ደረጃ በዘርፉ መነቃቃት መፈጠሩን የተናገሩት ሃላፈው ሁሉም በሁሉም ዘርፍ በማምረት ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የሚፈለገውን ውጤት እንዲመጣ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህን መነሻ በማደረግም ክልሉ የኢንደስትሪ ማእከል ለማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩና ለስኬታማነቱንም መስረተ ልማት የማሟላትና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በመሆናቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል ዶ/ር አባስ መሃመድ። በመሆኑም በክልሉ በተለያዩ የኢንደስትሪ አማራጮች ለሚሰማሩ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር መሬት ወስደው ስራ ያልጀመሩ ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውና ይህ ከልሆነ ግን በኢንቨስትመንት ህጉ መሰረት እረምጃ እንደሚወሰድም አሳስበዋል። መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ላይ ያስቀመጠውን ስትራቴጂክ እቅድ ውጤታማ ለማድረግ እና ብሎም በአምራች ኢንደስተረው የሚታዩ የማምረት አቅም ማነስ፣ የግብአትና ሌሎችም ችግሮች በመቅረፍ ስኬታማ እንዲሆኑ ለማድረግ አቅም የፈጠረ ስልጠና መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊዎች ናቸው። አቶ ዘነበ ደበላ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንት እና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲሆኑ በኢንዱስትሪዎች አካባቢ ይስተዋላል የነበረው ከአቅም በታች የማምረት ሂደት የሚቀይርና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ኢንዲስትሪዎች ያስመዘገቡት ካፒታልና የሚፈጥሩት የስራ እድል ብቻ መሰረት ተደርጎ ክትትል ይደረግ እንደነበር የገለፁት ኃላፊው በቀጣይ ደግሞ አቅማቸው ተጠቅመው ማምረት እንዲችሉ ይደረጋል ብለዋል። ወ/ሮ ትርንጎ ጴጥሮስ የከንባታ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ቢሮው ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራ ያለው ሰራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ከስልጠናው ያገኙትን ግብዓት በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል።