በገቡት ውል መሰረት በማያለሙ ባለሃብቶች ላይ የሚወሰድ እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡
በ2017 በጀት አመት ብቻ ለኢንቨስትመንት ልማት የተረከቡትን መሬት በአግባቡ ባላለሙ 151 ፕሮጀክቶች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ ተወስዷል፡፡ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር አባስ መሐመድ እንዳሉት በክልሉ የተረከቡትን መሬት በአግባቡ በማልማት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ምስጋና የሚገባቸው ባለሃብቶች አሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግዴታቸውን ሳይወጡ መሬት አጥረው በማስቀመጥ ውስን የሆነውን የመሬት ሃብት ለብክነት የሚዳርጉ አሉ፡፡ በመሆኑም ባለፉት አመታት ስናደርግ አንደቆየነው ከማያለሙ ባለሃብቶች መሬት ነጥቀን ለሚያለማ ለሌላ መስጠታችንን እንቀጥላለን፡፡በክልላችን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማራችሁ ባለሃብቶች ይህን አውቃችሁ ልትሰሩ ይገባል፡፡መስራት የማትችሉ ደግሞ የተረከባችሁትን መሬት ለየዞኖችና ልዩ ወረዳዎች አስረክቡ ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት አመት በገቡት ውል መሰረት ማልማት ባለመቻላቸው የእርምት እርምጃ ከተወሰደባቸው 151 ፕሮጀክቶች መካከል 107 ማስጠንቀቂያ፣2 ፕሮጀክቶች መሬት መቀነስ እንዲሁም 42 ፕሮጀክቶች ላይ ውልና የኢንቨስትመንት ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ እንደሆነ ሃላፊው አብራርተዋል፡፡
በበጀት አመቱ እርምጃ የተወሰደባቸው ፕሮጀክቶች ቁጥር ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ106 ብልጫ ያለው መሆኑን ሃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡